የአንድዋለም ወንጀል አገሩን መዉደዱ ነው – አማኑኤል ዘሰላም

Andualemአቶ ብርሃኑ ወንድማገኝ በነአንዱዋለም አራጌ ላይ ክስ ያቀረበ አቃቤ ሕግ ነው። ይህ የሕግ ሰው ነኝ ባይ ካድሬ፣ በወያኔ ኢቲቪ ቀርቦ «አንዱዋለም አራጌን በተመለከተ፣ የግንቦት ሰባትን ተእልኮ ለማስፈጸም አገር ዉስጥ በሕቡእ (ስዉር) ይንቀሳቀሳል። በሰላማዊ ትግል እንታገላለን የሚሉ የፓርቲዎችን ሽፋን አድርጎ ሲንቀሳቀስ የነበረ በመሆኑ በቂ ማስረጃ አቅርበናል» ሲል ነበር የተናገረው።

አንዱዋለም ያደረጋቸው የነበሩ እንቅስቃሴዎችን በሙሉ ሲያደርግ የነበረው በግልጽና በገሃድ ነዉ። ለተለያዩ ፓልቶክ ክፍሎች፣ አገር ዉስጥና በዉጭ ለሚገኙ ሜዲያዎች በርካታ ቃለ መጠይቆችን ሰጥቷል። በአገር ቤት፣ በአንድነት ፓርቲ ዉስጥ ሆነ በተለያዩ ቦታዎች በተደረጉ ዉይይቶችና ስብሰባዎች ያቀረባቸው ንግግሮች በሙሉ የተደበቁ አይደሉም። ዉጭ ካሉ ኢትዮጵያዊያን ጋር ብዙ ጊዜ በስልክ ሃሳቦችን ተለዋዉጧል። በስልክ ያደረጋቸው ንግግሮችም፣ 24 ሰዓት የሰላማዊ ተቃዋሚ መሪዎችን ስልክ በሚጠልፈው ቴሌ ዘንድ የተሰሙ ናቸው። ቤቱና ቢሮዉ ከላይ እስከ ታች ተበርብረዉ ፣ የሚስጥራዊ የኮሚኒኬሽን መሳሪያዎች፣ ቦምቦች፣ ፈንጂዎች፣ ሚስጥራዊ ሰነዶች አልተገኙም። ኤሜሎቹ በሙሉ ተነበዋል። አንዱዋለምን ከግንቦት ሰባት ጋር የሚያገናኝ፣ በሕቡእ እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሆነ የሚያመለክት አንዳች መረጃ አቃቤ ሕግ አላቀረበም። መረጃዎች ቢኖሩ ኖሮ፣ «እንኳን ዘንቦብሽ ድሮም ጤዛ ነሽ» እንደተባለ፣ ዜጎችን በማዋረድና በማሳነስ የሚታወቀዉ የወያኔ ኢቲቪ፣ ይሄን በስፋት ያወራልን ነበር።

አንዱዋለም አራጌ ከታሰረ በኋላ አቃቤ ሕጎች መረጃ ማቅረብ ባለመቻላቸው፣ የዉሸት መረጃዎች ማሰባሰብ የግድ ሆነባቸው። የታሰሩ ሌሎች የአንድነት አባላትን ማግባባት ጀመሩ። «በአንዱዋለም ላይ እኛ ተናገሩ የምንላችሁን ከተናጋራችሁ እንፈታቹሃለን» ብለው እጆቻቸዉን ጠመዘዙ። ብዙዎች በአንዱዋለም ላይ የዉሸት መረጃ ማቅረቡ ሕሊናቸውን ስለከበደው ፍቃደኛ አልሆኑም። ነገር ግን ተስፋሁን አናጋው፣ የሚባል ደካማ ሰው ተገኘና የዉሸት ምስክርነት ቀረበ። እንግዲህ በአገዛዙ ካድሬዎች ተቀናብረው ከቀረቡ የዉሽት ምስክርነቶች ዉጭ፣ ቅንጣት የምታክል፣ አንዱዋለምን ሽብርተኛ ወይንም ከግንቦት ስባት ጋር የሚሰራ መሆኑን የሚያሳይ መረጃ አልቀረበም። ወያኔዎች በዉሽት ምስክርነት ነው የእድሜ ልክ እስራት የበየኑበት።

የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ለአገር ማሰብ፣ ለመብት መቆም፣ “አንዲት ኢትዮጵያ” ማለት ወንጀል የሆነበት ኢትዮጵያ ናት። ብርቅዬ የተማሩ፣ ከራሳቸው ይልቅ ለሌሎች የሚያስቡ ልጆቿ ወደ ወህኒ የሚወረወሩባት አገር ናት። አሳዛኝ አገር ሆናለች።

Free Andualemሆኖም ተስፋ የሚሰጡ ብዙ ነገሮች እየታዩ ነው። አንዱዋለም አራጌ ቢታሰርም፣ እጅግ በጣም ብዙ አንድዋለም አራጌዎች ፈርተዋል። እንደ ሃብታሙ አያሌው፣ ዳንኤል ሺበሺ፣ አንጋው ተገኝ፣ ገበየሁ ሲሳይ፣ ስንትየሁ ቸኮል፣ ሃዲያ ሞሃመድ፣ መሳይ ተኩ ..የመሳሰሉ የአንድነት ሰዎች አንዱዋለም አራጌን በወህኒ ተቀላቅለዋል። ሆኖም ሌሎች ብዙ ከየቦታው እየተነሱ ነው። ታጋይ ቢታሰር ትግል አይቆምም። ጥቂቶችን በማሰር የነጻነትና የለዉጥ ጥያቄን ማፈን አይቻልም።
በመሆኑም ከአንዱዋለም አራጌ ጎን እንቆማለን። አላማው አላማችን ነው። እነርሱን “ሽብርተኛ” ቢሉትም ለኛ ወንንድማችን፣ ጀግናች፣ መሪያችን ነው። እኛም አንዱዋለም አራጌዎችን ነን። እርሱ በአካል ድምጹን ማሰማት ባይችልምም፣ እኛ እርሱን ሆነ የነጻነትና የፍትህ ድምጽ እንደ መብረቅ እናስተጋባለን።

አንድዋለም አራጌና ሌሎች ጀግኖቻችን በሙሉ እስኪፈቱ፣ አገራችን ኢትዮጵያም ራሷ እስክትፈታ ትግሉ ይቀጥላል!

Filed in: News
Find us

You might like:

ዛሬ የጀግናው አንዷለም አራጌ የትውልድ ቀን ነው  7 አመት እስር ቤት ልደቱን አከበረ ዛሬ የጀግናው አንዷለም አራጌ የትውልድ ቀን ነው 7 አመት እስር ቤት ልደቱን አከበረ
UN Declares Detention of Opposition Politician Andualem Aragie Arbitrary; Calls for Release UN Declares Detention of Opposition Politician Andualem Aragie Arbitrary; Calls for Release
በግፍ የተገፋው የአማሮቹ ልጅ!! እንደ ኢትዮጲያዊነቱ ታግሎ ሳለ በአማራነቱ መከራው የበዛበት አንዱአለም አራጌ! !!! በግፍ የተገፋው የአማሮቹ ልጅ!! እንደ ኢትዮጲያዊነቱ ታግሎ ሳለ በአማራነቱ መከራው የበዛበት አንዱአለም አራጌ! !!!
ትውስታ” ልክ የዛሬ 7.አመት አካባቢ ቀበና የሚገኘው የቀድሞ አንድነት ፓርቲ ጽ/ቤት ግቢ – ስንታየሁ ቸኮል ትውስታ” ልክ የዛሬ 7.አመት አካባቢ ቀበና የሚገኘው የቀድሞ አንድነት ፓርቲ ጽ/ቤት ግቢ – ስንታየሁ ቸኮል

Leave a Reply

Submit Comment

© 4850 Free Andualem Aragie. All rights reserved. / Valid.
Proudly designed by www.freeandualemaragie.org.